ማለዳ ተነስተን እያንዳንድን እለት ስንቀበል ከእያንዳንዲቷ ቀን ጋር የተለያዩ ፈተናዎችን ወደ ኋላ ከሚጎትቱ ነገሮችን ጋር ፊት ለፊት እንገናኛለን፡፡ነገሮች ባሰብነው መንገድ ሳይሄድ ሲቀሩ በእግዚአብሔር ላይ ያለን መታመን ውሃ አፈርን እንደሚሽረሽር እንዲሁ ቀስ እያለ ተሸርሽሮ ሲሄድ አይኖቻችን ከእግዚአብሔር ላይ ተነስተው በዚህ አለም ነገር ላይ ሲያርፍ የሰዎችን ስኬትና ደስታ አይተን ራሳችንን ስንመለከት ግን ባዶነት እና ብቸኝነታችን ጎልቶ ሲታየን የውስጣችን ሰላም ጠፍቶ እርሱን ፍለጋ በምድረበዳ ስንቅበዘበዝ እግዚአብሔር የተወን የሌለ ሲመስለን ሀልዎቱ ከእኛ ተለይቶ እንደሄ ሲሰማን እርሱ ግን አሁንም በዙፋኑ ላይ አለ እርሱ ከእስትንፋሳችን የልቅ ቅርባችን ነው፡፡
አይናችንን ግን ዳግመኛ ወደ እርሱ ስንመልስ እርሱን ብቻ ስንመለከተው ከተራራዎቻችን በላይ ታላቅነቱን ያሳየናል፡፡እርሱ ትልቅ ነው ታላቅነቱ በቃላት የማይገለፅ ሃያልና የሁሉ ባለቤት እና ፈጣሪ በወደደው መንገድ ሁሉንም የሚመራ ነው፡፡ እንደዚህ ታላቅ ሆኖ ሣለ ለእኛ ቅርብ ነው ስለእያንዳንዳችን ማሰቡ ግድ የሚለው አባት መሆኑ እንዲሁም ከመፈጠራችን በፊት የህይወታችንን ቀናት በልዩ ጥበቡ ማቀድ እና ማስቀመጡን ስናስብ ሁኔታችንን እንረሳዋለን ለቀነው የነበረውን የተስፋውን ቃል አጥብቀን እንይዘዋለን የዛሬውን ጥያቄያችንን ሳይሆን ከእኛ ሃሳብና እቅድ በላይ የሆነውን ታላቁን የእርሱን አላማና ሃሳብ መመልከት እንጀምራለን፡፡
“ያልተሠራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ፤ የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ አንድ ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍህ ተጻፉ።” — መዝሙር 139፥16
እግዚአብሔር ባልጠበቅነው መንገድ በቃሉ ያፅናናል፣ይፈውሰናል ለልባችን ይናገረናል።ይህም በልባችን ወስጥ ያለውን አለማመን አስወግዶ ውስጣችንን በእምነትና ተስፋ ሞልቶ ጉልበታችን በአምላካችን ፊት ይምበረከካል አንደበታችን በውስጣችን የገባውን ፍቅሩንና ምህረቱን ለመዘመር ቅኔን ይቀኛል፡፡ አቤቱ እግዚአብሔርን ተስፋ ማድረግ ምንኛ ትልቅ ነገር ነው፡፡
ያዕቆብ ሆይ፤ ለምን እንዲህ ትላለህ? እስራኤል ሆይ፤ ለምን እንዲህ ትናገራለህ? “መንገዴ ከእግዚአብሔር ተሰውራለች፤ ፍርዴም በአምላኬ ቸል ተብላለች” ለምን ትላለህ? አታውቅምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፣ የምድር ዳርቻ ፈጣሪ ነው። አይደክምም፤ አይታክትም፤ ማስተዋሉም በማንም አይመረመርም። ለደከመው ብርታት ይሰጣል፤ ለዛለው ጒልበት ይጨምራል። ወጣቶች እንኳ ይደክማሉ፤ ይታክታሉም፤ ጐበዛዝትም ተሰናክለው ይወድቃሉ። እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን፣ ኀይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፤ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፤ አይደክሙም። ኢሳይያስ 40:27 - 31
Comments